የኤድመንተን ሰዓሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ፤ በኤድመንተን እና በአካባቢዋ በሚኖሩ ካህናትና ምዕመናን ሕብረት ታህሳስ 29 2006 ዓ.ም የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሚከበርበት ዕለት ተመሰረተ ።
ቤተክርስቲያኒቱ ስትመሰረት በወቅቱ ሁለት ካህናትና 35 የሚሆኑ ማኅበረ ምዕመናን ነበሩ ። በወቅቱ አንድ በጎ አድራጊ ምዕመን ለቤተክርስቲያኒቱ የሚያስፈልጓትን ንዋያተ ቅድሳት አሟልተዋል ። በዚያን ጊዜ የራሳችን የሆነ ህንጻ ቤተክርስቲያን ባለመኖሩ በኤድመንተን ከተመ የሚገኙ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትን በኪራይ እና ከክፍያ ውጪ እየተባበሩን አገልግሎቱ ቀጠለ ።
ከቀን ወደቀንም የምዕመናን ቁጥር እየጨመረ ሄደ ፤ ቤተክርስቲያናችንን እንድናቋቁም ፈቃድ የሰጡን ብፁዕ አባታችን አቡነ ማትያስ በካናዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ በመጋበዝ በጊዜአዊነት የምንጠቀምበት ቤተክርስቲያን ተባረከልን ። ግንቦት 1 ቀን የሚከበረውን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ልደትን (ግንቦት ልደታ)ታቦት ማንገስ ተጀመረ ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዓመት ሁለት ጊዜ ኅዳር 21 እና ግንቦት 1 ቀን ስርዓተ ንግሥ ማክበሩ ቀጠለ ።
የቤተክርስቲያን አምላክ እየረዳን ከዕለት ወደ ዕለት የምዕመናን ቁጥር እየጨመረ መጣ ። በኪራይና በትብብር የምንገለገልባቸው አብያተ ክርስቲያናት የአገልግሎት ጊዜ በሰዓት የተገደበ ነበረ ። ይህ ክስተት ካህናት ተረጋግተው እንዲቀድሱ ምዕመናንም ተረጋግተው እንዲያስቀድሱ ፤ እንዲጸልዩ ፤ እና እንዲዘምሩ የአዲስ ቤተክርስቲያን ግዢ እንዲፈጸም ሃሳብ ተወጠነ ።
በእግዚአብሔር ፈቃድ በቅድስት ድንግል እናቱ ረድኤት በአሁኑ ሰዓት የምንጠቀምበት (የምንገለገልበት)ህንጻ ቤተክርስቲያን (Ebenezer United Church)በ2015 ዓ.ም ግዢ ተፈጸመ ። በመሆኑም ህንጻ ቤተክርስቲያኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስርዓት መሰረት ውሳጣዊ ጥገና እና የቅርጽ ለውጥ ተደረገለት ። ከዚህ በማስከተል ነሃሴ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ጽላቱን ለማስገባት በአዲስ መልክ የቤተክርስቲያኒቱ ቅዳሴ ቤት ተከበረ ።
የአዲሱ ህንጻ ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤት የተከበረው ነሃሴ 24 ቀን የጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ኃይማኖት የዕረፍት በዓል በሚከበርበት ዕለት ነበር ። ይህ ክስተት አዲስ በረከት ይዞልን መጣ ። ይኸውም ማህበረ ካህናቱ ያቀረቡትን ጥያቄ በብፁዕ አባታችን አቡነ ማትያስ ተቀባይነት በማግኘቱ ታቦተ ተክለ ኃይማኖትን ደርበውልን በየዓመቱ የቤተክርስቲያናችን ቅዳሴ ቤት የጻድቁ አባታችን ታቦትን ነሃሴ 24 ቀን በማክበር (በማንገስ)የሚከበር ሆነ ።
በአሁኑ ሰዓት የኤድመንተን ሰዓሊተ ምህረት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን ከ350 በላይ የሚሆኑ ቋሚ አባላት አሏት ። በየሳምንቱ ዘወትር እሁድ እሁድ በየወሩ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዕለት ሥርዓተ ቅዳሴ ይካሄዳል ። እንዲሁም በተለያዩ ቅዱሳን ዓመታዊ በዓላት ሥርዓተ ቅዳሴ ይከናወናል ። ዘወትር ዓርብ የሰርክ ጸሎት (መሃረነ አብ)የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ይሰጣል ። ዘወትር ቅዳሜ ከ10am እስከ 12pm የአብነት ትምህርት ዘወትር እሁድ ከ2 እስከ 3pm የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይሰጣል ። ወደፊትም አገልግሎቱን ለአጥቢያውና ለአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ተደራሽ የማድረግ እቅድ አለን ።