የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ

ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ባንድ አምላክ በእግዚአብሔር ማመን የጀመረችው ቀዳምዊ ምኒሊክ የአባቱ የሶሎሞንን ሀገር ኢየሩሳሌምን ጎብኝቶ ሲመለስ የሙሴን ጽላትና ካህናተ ኦሪተን፣ በርካታ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ከሊቆቻቸው ጋር ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ካመጣበት ጊዜ እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ። በተጨማሪም በ586 ዓመት ከጌታ ልደት በፊት ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን በመቃጠሏ ከግዞት የሸሹ እሥራኤላውያን በዮናታን መሪነት ወደግብጽ ከተሰደዱት ተከፍለው ወደ ኢትዮጵያ እንደ መጡ እና ሃይማኖታቸውንና ሥርዓታቸውን እንዳስፋፉ ይነገራል። ሀገራችን ኢትዮጵያ ከክርስትና በፊት ብሉይ ኪዳንን ለመቀበሏ በታሪክ እና በጽሑፍ ከተነገሩት በተጨማሪ የኦሪት ልማዶች በህዝቡ ዘንድ ልማድ እና ባህል ሆኖ መኖሩ አስረጅ ነው። ከእንዚህም ውስጥ በኦሪት እንዳይበሉ የተከለከሉትን እንስሳት እና አዕዋፍ ዛሬም ድረስ አለመብላታችን እንዲሁም የወንዶች ግርዛት ምሳሌዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ ክርስትናን የተዋወቀችው በሐዋርያት ሥራ 8፣26 ላይ እንደተገለጠው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በፊልጶስ በ34 ዓመተ ምህረት ተጠምቆ ወደ ሀገሩ በተመለሰ ጊዜ ነው። በአራተኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ታላቁ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ አውሳቢዮስ “የኢትዮጵያው ጃንደረባ ጥምቀት በዓለም የመጀመሪያው የክርስትና እምነት ፍሬ” ብሎታል። ይሁን እንጂ ክርስትና የመንግሥት እምነት ሆኖ በኤጲስ ቆጶስ ደረጃ መመራት የጀመረው በአራተኛው ክፍለ ዘመን በአክሱም ዘመነ መንግሥት እንደሆነ ይተረካል። ንጉሥ ኤዛና በገንዘቦቹ ላይ የነበሩትን የጨረቃ ሥዕልን ቀይሮ የመስቀል ምልክት በማድረግ በዓለም ከነበሩት ነገሥታቶች  መካከል ቀድምትነትን ቦታ አግኝቷል። በ356 ዓ.ም.  አርያናው ንጉሥ ኮንስታንትዩስ ለአክሱም ንጉሥ ሲጽፍ “ጳጳሱ ፍሬሚናጦስ የክርስትናን እምነት አጥፊ ስለሆነ ወደ ሮም ተይዞ ይላክ”

ይሁን እንጂ ሥርዓተ ክርስትናን በትምህርት ያጠናከረው በእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ አትናቴዎስ በተሾመው በመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ በፍሬምናጦስ ወይም አባ ሰላማ ነው ። ኢትዮጵያ ከሌሎች በተለየ ብሉይን ከሐዲስ አስተባብራ የያዘች የእግዚአብሔር የምስጢር ሀገር ናት። በመጽሐፍ ቅዱስም ስሟ ከአርባ ጊዜ በላይ ተንስቷል። ለምሳሌ ያህል በነቢዩ ዳዊት «ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች» (መዝ. 67(68)፥31) እንዱሁም በኦሪት ዘፍጥረት (ዘፍ 2፥13) “የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ነው፣እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል።” ከመጽሐፍ ቅዱስ በተጨማሪ በአያሌ የታሪክ መዛግብትና መጽሐፍት ላይ ስለ ኢትዮጵያ ተዘግቧል ይገኛል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከስድስቱ የኦርየንታል ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክሪስቲያናት ማለትም ከኮፕት (ግብጽ)፣ ህንድ፣ ሶርያ፣ አርመንና ኤርትራ አንዷ ናት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ሊቃውንቶችና የተማሩ ቀሳውስቶች ያላት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ከሰላሳ ሺህ በላይ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ከሦስት መቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ ቀሳውስቶችና ወደ አርባ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ምዕመናን ያላት አገር ስትሆን በዚህም ከምሥራቃውያን የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ አገሮች በምዕመናን ብዛት የቀዳሚነትን ሥፍራ ይዛለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሦስቱን ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ብቻ ትቀበላለች እነርሱም የኒቅያው ጉባኤ (325 ዓ.ም.) የኤፌሶን ጉባኤ (381 ዓ.ም.) የቁስጥንጥንያ ጉባኤ (431 ዓ.ም.) ናቸው። ስለዚህ ሁለቱ ጉባኤዎች ያወጧቸው ጸሎተ ሃይማኖትን ተቀብላለች።

የክርስትና በኢትዮጵያ መስፋፋት

የክርስትና እምነት እና ሥርዓት በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ጉልህ አስተዋጽዖ ካበረከቱ ቅዱሳን መካከል ቅዱስ ፍሬምናጦስ (አባ ሰላማ)፣ ቅዱስ ያሬድ፣ ቅዱስ ላልይበላ፣ ዘጠኙ ቅዱሳን (ተሰዓቱ ቅዱሳን) እና አቡነ ተክለ ኃይማኖትን ዋናዎቹ ናቸው።

ቅዱስ ፍሬምናጦስ (አባ ሰላማ)

በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን “ቅዱስና ያለ ተንኰል የሚኖር ነውርም የሌለበት ከኀጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ያለ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል” (ዕብ.፯፣፳፮) ብሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ሊቀ ካህናትነት እንደተናገረው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ከሾማቸው ከሐዋርያት ሐረገ ክህነት ተያይዞ የመጣ የሐዋርያት ተከታይ የሆነ ሊቀ ካህናት ማግኘት ይገባኛል ብላ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እንዲያስመጣላት ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማን ወደ እስክንድርያ ላከች፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ የእስክንድርያ ፓትርያርክም ራሱኑ ሾሞ ላከው፡፡ ኢትዮጵያ ክርስትናን የተቀበለችው በመጀመሪያው ምዕት ዓመት ይሁን እንጂ በሲኖዶስ ሕግ የኤጲስ ቆጶስ መንበር የተሰጣት በአራተኛው ምዕት ዓመት በ፫፻፴ ዓ.ም. ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ተልኮ ሔዶ ከእስክንድርያው ፓትርያርክ ከቅዱስ አትናቴዎስ ዘንድ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሾሞ በመጣው በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መምህርነት በአብርሃና በአጽብሐ ዘመነ መንግሥት ጊዜ የክርስትና ሃይማኖት በዐዋጅ ተሰብኳል፡፡ ቅዱስ አባ ሰላማ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መንበረ ጵጵስናውን አክሱም ላይ አድርጎ በሀገራችን የወንጌልን ብርሃን በሰፊው ስለገለጠ ከሣቴ ብርሃን ተባለ፡፡ በዚሁ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የታወቀች ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ለመሆን መብቃቷን ታሪክ ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከጥንታዊት የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሥርዐተ እምነት አንድነትና የእህትማማችነት ህብረት ስለነበራት ግብፃውያን ጳጳሳት ሥልጣነ ክህነት በመስጠት ብቻ ተወስነው የቀረው የአስተዳደሩና የውስጥ አመራሩ ይዞታ ግን በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ይካሄድ ነበር፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያናችን በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ፣ በሥርዐተ ትምህርትና በባህል ራሱን የቻለ አቋም የነበራትና ያላት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ

ቅዱስ ያሬድ ሚያዝያ ፭ ቀን ፭፻፶፭ ዓ.ም በአከሱም ከተማ ተወለደ፤ ዜማውንም ከ፭፻፵-፭፻፷ ዓ.ም አዘጋጀ፤ ግንቦት ፲፩ ቀን ፭፻፸፩ ዓ.ም በሰሜን ተራራዎች በጸለምት ዋሻ ውስጥ ተሠወረ፡፡ ቅዱስ ያሬድ የግእዝ፣ እዝልና አራራይ ዜማዎችን ከሦስት ወፎች /መላእክት በወፎች ተመስለው/ መማሩን ሊቃውንት ይገልጣሉ፡፡ እነዚህ መላእክት እየመሩት ወደ አርአያም አርጎ የ፳፬ቱን ካህናተ ሰማይ ዜማ ከተማረ በኋላ ጠዋት በ፫ ሰዓት በአክሱም ቤተ ክርስቲያን “ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሣረረ ወበዳግመ አረአዮ ለሙሴ ዘከመ ይግበር ግብራ ለደብተራ” ብሎ አዜመ፡፡ የቅዱስ ያሬድ የመጀመሪያ ዜማው “አርያም” በመባል ይታወቃል፡፡ ይህም ከመላእክት ወይም ከሰማይ የተገኘ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ዜማን ከማበርከቱም ሌላ በትምህርት ሂደትም አስተዋጽዖ አድርጓል፤ የድጓን፣ የጾመ ድጓን የዝማሬ መዋሥዕትንና የቅዳሴን ትምህርት ከማስተማሩም በላይ ለቅኔ ትምህርትም መሠረት ጥሏል፡፡ ዜማውን ካዘጋጀ በኋላ ለ፲፩ ዓመታት እስከ አርባ ምንጭ ድረስ ዞሮ አስተምሯል፡፡

ቅዱስ ላልይበላ

ቅዱስ ላልይበላ ታህሳስ ፳፱ ቀን ፲፻፹ ዓ.ም ተወለደ፤ ሰኔ ፲፪ ቀን ፲፪፻፯ ዓ.ም አረፈ። በተወለደ ጊዜ በንብ ስለ ተከበበ እናቱ ማር ይበላል ለማለት “ላል ይበላል” ብላዋለች። ቅዱስ ላልይበላ የብሉያትንና የሐዲሳትን ትምህርት ትርጓሜ የተማረና ጠንቅቆ የሚያውቅ ነው። ቅዱስ ላልይበላ የኢትዮጵያ ንጉሥ የነበረ ሲሆን፤ ስመ ንግስናውም አፄ ገብረ መስቀል ነበር። ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ያሰራ ሲሆን በከተማው በደብረ ሮሃ ዓለምን ያስደነቁና ከታች የተዘረዘሩትን ¬፲፩ አብያተ ክርስቲያናትን በመላዕክት አጋዥነት ከቋጥኝ ፈልፍሎ ሠርቷል።

፩. ቤተ አማኑኤል ፭. ቤተ ገብርኤል ፱. ቤተ መርቆሬዎስ ፪. ቤተ መድሃኔዓለም ፮. ቤተ መስቀል ፲. ቤተ ሊባኖስ ፫. ቤተ ማርያም ፯. ቤተ ጎልጎታ ፲፩. ቤተ ደናግል ፬. ቤተ ሚካኤል ፰. ቤተ ጊዮርጊስ

 

ዘጠኙ ቅዱሳን

ዘጠኙ ቅዱሳን በኬልቄዶን ጉባኤ ምክንያት በተዋሕዶዎች ላይ በአውሮፓ፣ በእስያና በመካከለኛው ምሥራቅ በተነሣው ፈተና የተነሳ ከሮም፣ ከእስያ፣ ከአንጾኪያ፣ ከቁስጥንጥንያ፣ ከቂሳርያና ከኪልቂያ በስደት የመጡ ናቸው። ስማቸውም አባ አሌፍ፣ አባ አረጋዊ፣ አባ ጰንጠሌዎን፣ አባ ገሪማ፣ አባ ጵሕማ፣ አባ አፍጴ፣ አባ ሊቃኖስ፣ አባ ይምዓታ እና አባ ጉባ ይባላሉ። ዘጠኙ ቅዱሳን በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ሲሆን በተለይም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አጽንተዋል፣ የተለያዩ መጽሐፍትን ተርጉመዋል፣ ስብከተ ወንጌልን አስፋፍተዋል፣ በርካታ ገዳማትን መስርተዋል፣ ሥርዓተ ምንኩስናን አደራጅተዋል።

አቡነ ተክለኃይማኖት

አቡነ ተክለኃይማኖት ታህሣሥ ፳፬ ቀን ፲፩፻፹፮ ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ቡልጋ ጽላልሽ ተወልደው ነሐሴ ፳፬ ቀን ፲፪፻፹፮ ዓ.ም አርፈዋል። በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ሥላሴን አመስግነዋል። ኢትዮጵያን ዞረው ወንጌልን ከማስተማራቸውም በላይ ሕዝቡን ከባዕድ አምልኮ ወደ ክርስትና በመመለስ ይታወቃሉ። አቡነ ተክለኃይማኖት ክንፍ የተሰጣቸው ብቸኛው ጻድቅ ሲሆኑ በብርሃን ሠረገላ ይጓዙ እንደነበር ገድላቸው ይናገራል። የግብጽ ክርስቲያኖች ለጻድቁ አባታችን ልዩ ፍቅር ያላቸው ሲሆን በስማቸው አብያተ ክርስቲያኖች ተክለዋል።

ዕምነት

 “ሁሉን በያዘ ሰማይንና ምድርን የሚታይና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር እናምናለን። ዓለም ሳይፈጠር ከርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ   በኢየሱስ ክርስቶስም እናምናለን። ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፤ የተፈጠረ ያይደል የተወለደ፤ በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል።

ሁሉ በርሱ የሆነ ያለ እርሱ ግን ምንም የሆነ የለም። በሰማይም ያለ በምድርም ያለ።ስለእኛ ስለሰው ስለ መዳኛችን ከሰማይ ወረደ። ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ከቅድስት ማርያም ፈጽሞ ሰው ሆነ።ሰው ሆኖ በጰንጤናዊ በጲላጦስ ዘመን ስለእኛ ተሰቀለ። ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረም፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በቅዱሳት መጽሐፍት እንደ ተጻፈ።በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ። ዳግመኛ ሕያዋንን ሙታንንም ይገዛ ዘንድ በጌትነት ይመጣል። ለመንግሥስቱም ፍጻሜ የለውም። ጌታ ማሕየዊ በሚሆን ከአብ በሠረፀ በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን። እንሰግድለት እናመሰግነውም ዘንድ፤ ከአብና ከወልድ ጋር በነብያት የተነገረ።

ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰብዋት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እናምናለን።ኃጥያትን ለማስተሥረይ በአንዲት ጥምቀት አናምናለን።የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን የሚመጣውንም ሕይወት ለዘላለሙ አሜን።”